Beliefs/እምነት


የአምነት መግለጫ

1.መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ እና ሐዲስ ኪዳን በምልዓት በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተፃፈ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን እናምናለን።እንዲሁም ሊታመንበት የሚገባው ሰው እምነት እና ሕይወት ላይ የመጨረሻ ሥልጣን ያለው፣ የቤተ ክርስቲያን እምነት እና ሥርዓት መሠረት እርሱ ብቻ መሆኑን እናምናለን።
2. በዘላለማዊ ፣ በማይወሰን ፣ የሚታየውን እና የማይታየውን ሁሉ በፈጠረ ፍፁም በማይለወጥ እና በሦስትነት እራሱን በገለጠ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ እናምናለን።
3. ኢየሱስ የእግዚአብሔር አብ ልጅ መሆኑን ፣በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ተፀንሶ ከድንግል ማሪያም መወለዱን ፣ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው መሆኑን ፣ ስለ ኃጢያታችንም በመስቀል የተሰቃየና የሞተ የተቀበረ ፣ በሦስተኛው ቀን ከሞት በአካል ተነስቶ ለሰዎች ተገልጦ በክብር ወደ ሰማይ ያረገ መሆኑን ፣አሁንም በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ዘወትር ለእኛ እንደሚማልድልን ፣ ዳግመኛም በታላቅ ክብር እና ሥልጣን እንደሚመለስ እናምናለን።
4. መንፈስ ቅዱስ አፅናኝ ፣ መንፈሳዊ አባቶችን ፣ ሐዋሪያትን ያንቀሳቀሰ እና የመራ ፣በአማኞች ውስጥ አድሮ መንፈሳዊ ስጦታዎችን እና ኃይልን በማከፋፈል ቤተ ክርስቲያንን እንደሚቀድስ እና ዓለምንም ስለኃጢያት ፣ ስለ ጽድቅ እና ስለ ፍርድ እንደሚወቅስ እናምናለን ። በተጨማሪም በኤፌሶን 5: 18 መሠረት የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ዛሬም አማኞች በፀሎት እና በጉጉት ሊጠብቁት እንደሚገባ በክርስቶስ የተሰጠ ትእዛዝ መሆኑን እናምናለን። ከላይ በተጠቀሰው መሠረት ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሚጠመቁ እና በልዩ ቋንቋ (ልሳን) እንዲናገሩ እንደሚያስችላቸው እናምናለን።
5. ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ያለ ኃጢያት መፈጠሩን በኋላም በፈቃዱ በኃጢያት መውደቁንና ውድቀቱም የኃጢያት ባህሪ ይዞ እንዲወለድ እንዳደረገው ፣ በዚህ ምክኒያት የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ ያለበት በደለኛ መሆኑን እናምናለን።
6. ለሰው ደኅንነት በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን በፀጋ ብቻ የሚገኝ እንጂ በሌላ በማንም ወይንም በምንም እንደማይገኝ እናምናለን ። ስለሆነም ሰው በኃጢያቱ ተጸጽቶ ንስሃ ቢገባና ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኙ እና ጌታው አድርጎ ቢቀበል ከመንፈስ ቅዱስ እንደሚወለድ እና የእግዚአብሔር ልጅነትን ሥልጣን እንደሚቀበል እናምናለን።
7. በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በሚደረግ በአማኝ የውሃ ጥምቀት እናምናለን ።
8. ጌታ ስለ እኛ እንደሞተ የምናስታውስበትን እና እንዲሁም ጌታ እስኪመጣ ሞቱን ለመናገር እና ከምእመናን ጋር ያለውን ሕብረት ለመግለጥ የጌታን እራት እንደምንካፈል እናምናለን ።
9. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንግስቱን ለመመስረት እንደገና እንደሚመጣ ፣ ሙታንንም እንደሚያስነሳና ለዘላለም በሚኖሩት እና በሚሞቱት ላይ ፍርድን እንደሚሰጥ ፣ ኃጢያተኞች ከእግዚአብሔር ፊት ተለይተው በገሃነም እሳት እንደሚሰቃዩ ፣ ጻድቃን ግን ከእርሱ ጋር በዘላለም ሕይወት በደስታ እንደሚኖሩ እናምናለን ።